የተሽከርካሪ ዋስትና (Motor Insurance)

ይህ ውል ለማንኛውም በሜካኒካል ኃይል ለሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ የሚያገለግል ሲሆን በሚከተሉት አማራጮች የዋስትና ሽፋን ይሰጣል፡፡

 • በ3ኛ ወገን ላይ ለሚደርስ ጉዳት ብቻ የሚሰጥ ዋስትና
 • የእሳት አደጋና ስርቆትን ጨምሮ በ3ኛ ወገን ላይ ለሚደርስ ጉዳት ዋስትና
 • የ3ኛ ወገን አስገዳጅ ዋስትና እና
 • ሙሉ የተሽከርካሪ ዋስትና

       1 በ3ኛ ወገን ላይ ለሚደርስ ጉዳት ብቻ የሚሰጥ ዋስትና

ይህ የውል ዓይነት መድን የተገባለት ተሽከርካሪ ወይም የተሽከርካሪው ጭነትና አባሪ ዕቃዎች በግጭት፣ በመገልበጥ፣ በእሳትና ፍንዳታ ምክንያት በ3ኛ ወገን ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ የሚደርስ ውድመትን ተከትሎ ለሚነሳ ህጋዊ ተጠያቂነት ዋስትና ይሰጣል፡፡ የዋስትና መጠን ወሰኑም እንደሚከተለው ነው፡፡

 • ለሞት፡- በሰው ከ5 ሺህ ብር ያላነሰና ከ40 ሺህ ብር ያልበለጠ
 • ለአካል ጉዳት፡- በሰው እስከ 40 ሺህ ብር ድረስ
 • ድንገተኛ ወይም አስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት፡- በሰው እስከ ብር 2 ሺህ
 • ሆስፒታል ውስጥ ለሚፈፀም የህክምና ወጪ፡- በሰው እስከ ብር 40 ሺህ ሆኖ ሞት ወይም የአካል ጉዳት ካለ ከጠቅላላ ክፍያ ላይ ተቀናሽ ይሆናል፡፡

በውሉ የማይሸፈኑ ክስተቶች

 • የመድን ገቢው ተቀጣሪ ወይም የቤተሰብ አባል የሆነ ሰው ላይ ለሚደርስ የአካል ጉዳትና ሞት፤
 • መድን የገባው ሰው ንብረት ላይ እና መድን ገቢው በአደራም ሆነ በጊዜያዊነት በያዛቸው እና በእርሱ ቁጥጥር ስር ባሉ ንብረቶች ላይ ለሚደርስ ውድመት፤
 • መድን በገባው መኪናም ሆነ በጫነው ንብረት ክብደትና መንቀጥቀጥ/ንቅናቄ ምክንያት በመንገድ፣ በድልድይ እና በማንኛውም መሸጋገሪያ ላይ ለሚደርስ ውድመት፤
 • ከማንኛውም አስተላላፊ መንገድ አቅም በላይ በተገናኘ ሁኔታ እና ተሽከርካሪው ላይ ሹፌርና ረዳቱን ሳይጨምር በሌሎች ሰዎች የሚደረግ ዕቃ መጫንና ማውረድን ተከትሎ ለሚመጣ ኃላፊነት፤
 • ከተሽከርካሪው ላይ ከሚወጡ ጪስ እና የእሳት ብልጭታዎችን ተከትሎ ለሚመጣ ህጋዊ የ3ኛ ወገን ጉዳት ተጠያቂነት ናቸው፡፡

1.2.የእሳት አደጋና ስርቆትን ጨምሮ በ3ኛ ወገን ላይ ለሚደርስ ጉዳት ዋስትና

ይህ የውል ዓይነት ከላይ በቁጥር 1 የተጠቀሰው ሽፋን እንዳለ ሆኖ መድን የተገባለት ተሽከርካሪ በእሳትና በስርቆት ብቻ ለሚደርስበት ውድመት ተጨማሪ ሽፋን ይሰጣል፡፡

1.3.የሦስተኛ ወገን አስገዳጅ ዋስትና

 ይህ የውል ዓይነት የተሽከርካሪ አደጋ የ3ኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2005’ን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ ሲሆን በቁጥር 1 ከተጠቀሰው የውል ዓይነት ከሚለይባቸው መካከል አንዱ አደጋ የተከሰተበት ቦታ አዋጁ ላይ በትምህርተ ጥቅስ መንገድ ተብሎ በተገለፀው አግባብ ለምሳሌ፡- በማሳ፣ በግቢ ውስጥ የተገሰቱ አደጋዎችን አይሸፍንም፡፡ የድርጅቱ የኃላፊነት መጠን ከላይ በቁጥር 1 እንደተጠቀሰው ይሆናል፡፡

1.4.ሙሉ የተሽከርካሪ ዋስትና

ይህ የውል ዓይነት ከላይ በቁጥር 1 እና 2 የተጠቀሱትን ክስተቶች ጨምሮ በመድን ገቢው ተሽከርካሪ ላይ ከዚህ ቀጥሎ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ለሚደርስ ውድመት/ጉዳት ሽፋን ይሰጣል፡፡

 • ድንገተኛ የሆነ የመጋጨትና የመገልበጥ አደጋ
 • መብረቅና ፍንዳታ
 • በሌሎች ሰዎች በዕኩይ ተግባር ለሚደርስ ውድመት
 • በበራሪ አካላትና ድንጋይ ምክንያት እና
 • ተሽከርካሪው በመንገድ፣ በባቡር ወይም በውኃ ላይ ተጭኖ በሚጓዝበት ጊዜ ለሚደርስበት ጉዳት ከለላ ይሰጣል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በተሽከርካሪው የጭነት ቁጥር ልክ የተሳፈሩ እድሜያቸው ከ14 እስከ 65 የሚደርስ ተጓዦች ላይ በውሉ መሰረት የተሸፈነ ክስተትን ተከትሎ እስከ 3 ወር ድረስ ለሚመጣ የህክምና ወጪ፣ የአካል ጉዳትና ሞት ሽፋን ይሰጣል፡፡ የዋስትና መጠኑም እንደሚከተለው ነው፡-

 • ለሞት፡- በሰው ብር 10 ሺህ
 • ለቋሚ አካል ጉዳት፡- ውሉ ላይ በተጠቀሰው ዝርዝር መሰረት
 • ለጊዜያዊ ሙሉ የአካል ጉዳት፡- ብር 60 በሳምንት ሆኖ ጠቅላላ ጊዜው ግን ከ26 ሳምንት አይበልጥም፡፡
 • ለህክምና፣ ለመድኃኒትና ተያያዥ ወጪዎች፡- በእያንዳንዱ አደጋ በሰው ብር 2 ሺህ ድረስ

የዋስትና መጠን

 • በውሉ መሰረት የሚሸፈን አደጋን ተከትሎ ለሚመጣ የተሽከርካሪ ውድመት ድርጅቱ ተሽከርካሪውን የማስጠገን፣ በሌላ የመተካት ወይን በጥሬ ገንዘብ የጉዳቱን መጠን የመስጠት አማራጭ ይኖረዋል፡፡
 • የዓባይ ኢንሹራንስ የዋስትና መጠን ወሰን ማለትም መኪናውን ለማስጠገን ወይንም ለመተካት የሚያወጣው የካሳ መጠን ጣሪያ ሁሌም ቢሆን በአደጋው ሰዓት ካለው የገበያ ዋጋ ወይንም ደንበኛው መድን የገባበትን መጠን በማነፃፀር ከሁለቱ ያነሰው ይሆናል፡፡
 • የዋስትና መጠንን በሚመለከት በተቻለ አቅም ደንበኛው የመከታተልና ሁሌም ተሽከርካሪው የተገባለት የዋስትና መጠን ከገበያው ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
 • የተሽከርካሪው የፊትና የኋላ መስታውቶች በተባራሪ አካላት ለሚደርስበቸው ጉዳት ለብቻቸው የዋስትና መጠን ይቀመጥላቸዋል፡፡
 • ከዚህ በተጨማሪም እንደ ቴፕ፣ ራዲዮና ሲዲ የመሳሰሉት በውሉ ላይ ሽፋን የሌላቸው ሲሆን እንዲሸፈኑ ከተፈለገ ግን የዋስትና መጠናቸው እንዲሁ በቅድሚያ ለብቻ መገለፅ ይኖርበታል፡፡

የጥበቃና የማስጎተቻ መጪን በሚመለከት

 • በውሉ መሰረት ሽፋን የተሰጠውን ክስተት ብቻ ተከትሎ የመጣ ምክንያታዊ የማስጎተቻና የመጠበቂያ ወጪ ከጠቅላላ የመኪና ማስጠገኛ ወጪ እስከ 20% ድርጅቱ ሽፋን ይሰጣል፡፡

የማይገኙ ዕቃዎችን በሚመለከት

 • በውሉ መሰረት በተሸፈነ አደጋ ምክንያት መቀየር ኖሮበት ነገር ግን ገበያ ላይ ወይንም በዕቃው አስመጪ ድርጅት ውስጥ ላልተገኘ ዕቃ የአስመጪው ድርጅት የመጨረሻ የዋጋ ተመንን ሳይበልጥ ከተገቢው የመግጠሚያ ዋጋ ወጪ ጋር የሚሸፈን ይሆናል፡፡

የአደጋ መነሻና የተቀየሩ ዕቃዎች መዋጮ

 • ለእያንዳንዱ አደጋ ደንበኛው የተወሰነ የአደጋ መነሻ ድርሻ የሚሸፍን ሲሆን ይህም እንደተሽከርካሪው ዓይነት በድርጅቱ አሰራር መሰረት በቅድሚያ ውሉ ላይ ይገለፃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ራሱን የቻለ የአደጋ መነሻ ለፊትና ለኋላ መስታውቶች፣ ለቴፕና ሰዲ እና ለመሳሰሉትም ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡

በውሉ ሽፋን ውስጥ ስለማይካተቱ ክስተቶች

ከላይ በክፍል አንድ የማይሸፈኑ ሁኔታዎች ተብለው ከተጠቀሱት በተጨማሪ የሚከተሉት በሙሉ የተሽከርካሪ ሽፋን ውስጥ ከማይካተቱ ሁኔታዎች ውስጥ ይገኙበታል፡-

 • የተሽከርካሪ እርጅና፣ ዝገትና መሰል ነገሮች፣ የጎማ መቀደድና መፈንዳት፣ የተሽከርካሪ ኤሌክትሪካልና መካኒካል ብልሽት
 • ማንኛውም ዓይነት አደጋውን ተከትሎ የተረቋጠ ጥቅም
 • በመድን ገቢው ቤተሰብ ወይም ሰራተኛ የሚፈፀም ስርቆት ወይም መሰል ተግባራት
 • በተሽከርካሪው ላይ ለሚገጠሙ የሙዚቃ ማጫወቻ እና መሰል ነገሮች (በቅድሚያ ተገልፀው በተጨማሪ አረቦን ክፍያ ሊሸፈኑ ይችላሉ)
 • በአየር ላይ በሚበርሩ አካላት ምክንያት በሚመጣ ሞገድ የሚደርስ አደጋ
 • በተሽከርካሪው ላይ በተገጠሙ ደረጃቸውን ያልጠበቁ መለዋወጫዎችና ደረጃውን ባልጠበቀ ነዳጅ፣ ዘይትና ቅባቶች ምክንያት ለሚመጣ አደጋ
 • የተሽከርካሪ ቁልፍ መጥፋትን ተከትሎ ለሚመጣ ወጪ
 • የተሽከርካሪ ቁልፍ መኪናው ላይ ወይም ሌላ ቦታ ወይም ውስጥ ካለበቂ ክትትል በተተውበት ሁኔታ ለሚከሰት ስርቆት

የባለቤት ለውጥን በሚመለከት

 • የመኪናው ባለቤትነት ወደ ሌላ ሰው ከተላለፈና ሁኔታውም ለድርጅቱ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ከተገለፀ ብቻ ውሉ ባለቤትነቱ ለተላለፈለት ሰው ይቀጥልለታል፡፡

ተሽከርካሪው ላይ ስለሚደረጉ ለውጦች

ተሽከርካሪው መድን ከገባበት ሁኔታ በተለየ የሚደረጉ መሰረታዊ ለውጦች ለድርጅቱ መገለፅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሆኖ ሳይቀርና ወይንም ለውጡ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ነገሮች ምክንያት አደጋ ቢከሰት ድርጅት ለመሸፈን አይገደድም፡፡

በተሽከርካሪ ዋስትና ላይ ስለማይሸፈኑ አጠቃላይ ነገሮች

በተሸከርካሪ ዋስትና ከማይሸፈኑ ሁኔታዎች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

 • ተሽከርካሪው ውሉ ላይ ከተገለፀው አገልግሎት ውጭ ጥቅም ላይ ከዋለ
 • አሽከርካሪው በመጠጥ ኃይል ወይም በአደንዛዥ ዕፅ ተፅዕኖ ካደረበት
 • አሽከርካሪው ህጋዊና ተገቢው የመንጃ ፈቃድ ሳይኖረው ሲቀር
 • እንደ ጎርፍ፣ አውሎ ነፋስ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ እሳተ ገሞራ እና የመሳሰሉትን የተፈጥሮ ክስተቶች ተከትሎ የሚመጣ ጉድለት ወይንም ኃላፊነት
 • ከጦርነትና መሰል ሁነቶች ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ጉዳት
 • ተሽከርካሪው ከተፈቀደለት የጭነት መጠን በላይ ሲጭን ለሚደርስ ጉዳትና ኃላፊነት
 • በውኃ፣ በበረዶ ወይም በጭቃ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወይ በከፊል በመስጠም ለሚመጣ ውድመት
 • ህገወጥ የሆኑ ድርጊቶችን ተከትሎ ለሚመጣ ውድመትና ኃላፊነት

በደንበኛው ሊጠበቁ የሚገባቸው አጠቃላይ ነገሮች

 • ደንበኛው የመድን ውሉን ሙሉ ሁኔታዎች ማክበር ይኖርበታል
 • ደንበኛው ለተሽከርካሪው ሁልጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል
 • ከተሽከርካሪ ዋጋ ትመና ጀምሮ የሚከሰቱ ማናቸውም ዓይነት ተገቢ ያልሆኑ ባህሪያት የውሉን ተፈፃሚነት ሊያስቀሩ ስለሚችሉ ደንበኛው ከዚህ ድርጊት መቆጠብ ይኖርበታል፡፡

በአደጋ ጊዜ መደረግ ስላለባቸው ሁኔታዎች

 • ደንበኛው አደጋ በደረሰ ጊዜ በተቻለ ፍጥነት ለድርጅቱ በፅሑፍ ማሳወቅ ይኖርበታል
 • ለሚመለከተው የፖሊስ/የፀጥታ አካል ሁኔታውን ማሳወቅና ክትትል እንዲደረግ መከታትል
 • በተሽከርካሪው ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ መጠበቅ/መከላከል
 • አደጋውን በሚመለከት ድርጅቱ በማያውቀው መልኩ ድርድር ወይንም መሰል ነገሮችን ከማድረግ መቆጠብ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ውል ስለማቋረጥ

 • ደንበኛው በማንኛውም ጊዜ ውሉን ማቋረጥ ሲችል ድርጅቱ ደግሞ የ15 ቀናት የቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ውሉን ማቋረጥ ይችላል፡፡

ማሳሰቢያ፡- ይህ ፅሑፍ ስለ ዋስትናው አይነት ማብራሪያ ለመስጠት የቀረበ እንጂ በሕግ ፊት የሚፀና ውል አይደለም፡፡