የዕቃ ጭነት ዋስትና (Marine Cargo Insurance)

የዕቃ ጭነት ዋስትና ዕቃው በተለያዩ የመጓጓዣ አካላት ተጭኖ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ ለሚደርስበት አደጋ እንደተገባው የውል ዓይነት ሽፋን ይሰጣል፡፡ ይህ ዋስትና በሦስት ዓይነት መልክ ሊሰጥ  ይችላል፡፡፡ እነዚህም፡-

 • በባህርና በየብስ ለሚጓጓዝ ንብረት
 • በየብስ ላይ ብቻ ለሚጓጓዝ ንብረት እና
 • በአየር ላይ ለሚጓጓዝ ንብረት

1. በባህርና በየብስ ላይ ለሚጓጓዝ ንብረት ዋስትና

ይህ ውል ንብረቱ ከሚመጣበት አገር ወደብ መርከብ ላይ ተጭኖ ጉዞ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በባህር ላይ በጉዞ ላይ እያለ ከዚያም ወደብ ላይ (ጅቡቲ ወደብ) ተራግፎ በተሽከርካሪ ላይ ተጭኖ እስከ ደንበኛው መጋዘን ወይም የማቆያ ቦታ እስኪደርስ ድረስ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ውሉ የማይሸፍናቸው ክስተቶችን ሳያካትት በአጠቃላይ ንብረቱ ላይ ለሚደርስ ውድመት ሽፋን ይሰጣል፡፡

በውሉ የማይሸፈኑ ክስተቶች

 • የመድን ባለመብቱ (መድን ገቢው) እያወቀ በሚያጠፋው ጥፋት ምክንያት/ተያያዥነት ለሚመጣ ጉዳት
 • ከጭነቱ/ከንብረቱ የተለመደና የሚጠበቅ ፍሰት፣ የክብደት/የቅርፅ መቀነስ/መቀየር፣ እርጅና እና መሰል ነገሮች ለሚመጣ ጉዳት
 • ደንበኛው/በሰራተኞቹ በተደረገ በቂ፣ ተገቢና ተመጣጣኝ ያልሆነ አጫጫንን ተከትሎ ለሚመጣ ጉዳት
 • ከንብረቱ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ጋር በተገናኘ መልኩ ለሚመጣ ጉዳት
 • በጉዞ መዘግየት ምክንያት ለሚመጣ ጉዳት
 • መድን ገቢው እያወቀው፣ ወይንም ሊያውቀው እየተገባ በአጓጓዦቹ መክሰር ወይም የገንዘብ ችግር ምክንያት ተያይዞ ዕቃው ላይ ለሚደርስ ጉዳት
 • ከአቶም ወይንም ከኒዩክሊየር መሳሪያዎች ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ለተፈጠረ ጉዳት
 • ደንበኛው እያወቀው ዕቃው/ንብረቱ ለጭነቱ በማይመጥን መጫኛ/ማጓጓዣ እና ኮንቴነር ላይ በመጫኑ ምክንያት ለሚመጣ ጉዳት
 • ከጦርነት፣ ጦር መሳሪያ እና መሰል ነገሮች ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ጉዳት
 • ከአሸባሪነትና ተያያዥነት ካላቸው ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ለሚመጣ ጉዳት
 • በሰራተኞች አመፅ፣ የስራ አድማና መሰል ክስተቶች ጋር በተገናኘ ለሚመጣ ጉዳት
 • ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ፣ የእምነት፣ እና መሰል ምክንያቶች ባሉት አካል/ሰው ለሚመጣ ጉዳት

 የውሉ የቆይታ/የዋስትና ጊዜ

የውሉ የቆይታ ጊዜ ዕቃው ከመነሻ ቦታው ከተጫነ በኋላ ይጀምርና ከሚከተሉት አንዱ ሲፈፀም  የሚያበቃ ይሆናል፡፡

 • በውሉ ላይ በተጠቀሰው ቦታ ዕቃው ተራግፎ ሲያልቅ
 • በውሉ ላይ ከተጠቀሰው ቦታ ውጪ ደንበኛው በመረጠው ሌላ ቦታ ዕቃው ተራግፎ ሲያልቅ
 • ውል ገቢው ወይንም ሰራተኞቹ ማንኛውንም ዓይነት የጭነት ተሽከርካሪ ወይንም ኮንቴነር እንደ ዕቃ ማስቀመጫ/መጋዝን መጠቀም ከፈለገ ወይም
 • ዕቃው ወደብ ላይ ከተራገፈበት ቀን በኋላ ያሉት 60 ቀናት ከተጠናቀቁ ውሉ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡

የካሳ ክፍያን በሚመለከት እና በአደጋ ጊዜ መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ

 • ድርጅቱ በውሉ መሰረት በሚሸፈን አደጋ ለሚመጣ ጉዳት ካሳ ይከፍላል
 • አደጋ በሚፈጠር ጊዜ ደንበኛው በሚቻለው አቅምና በተገቢው መንገድ የሚደርሰውን ውድመት ለመቀነስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
 • አደጋው/ጉዳቱ በሚፈጠርበት ጊዜ ደንበኛው ለድርጅቱ በአስቸኳይ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡
 • ለሚመለከተው አጓጓዥ/የወደብ አስተዳደር ስለጉዳቱ ማሳወቅና በፅሁፍ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተጎዱ ዕቃዎች እያሉ ለአጓጓዡ መልቀቂያ መስጠት አይገባም፡፡
 • ደንበኛው አደጋው/ክስተቱ በመርማሪዎች እንዲመረመር ማድረግ አለበት፡፡

በአደጋ ጊዜ የሚያስፈልጉ ዶክመንቶች

 • ዋናው የመድን ውል
 • የመርከብ/የጭነት ማጓጓዣ ሰነዶች
 • ዋናው ቢል ኦፍ ሎዲንግ
 • የአደጋ/የጉዳት ምርመራ ሪፖርት
 • የመርከብ፣ ወደብ መድረሻ ማረጋገጫ ቅፅ
 • የላኪው/የአምራቹ የዋጋ መቅረቢያዎች እና የመጫኛ ሰነዶች
 • ዕቃ አጓጓዦችና መሰል አካላት ጋር ተጠያቂነታቸውን በሚመለከት የተደረጉ የፅሑፍ ልውውጦች እና ሌሎች በመድን ሰጪው የሚጠየቁ ሪፖርቶች

2.  በአየር ላይ ለሚጓጓዙ ንብረቶች ዋስትና

ይህ የዋስትና ዓይነት የሚሰጠው ሽፋን ከላይ በቁጥር አንድ እንደተጠቀሰው ይሆንና የውል ጊዜው ግን እንደሚመለከተው ይሆናል፡፡

 • መድን የተገባለት ዕቃ ከሚነሳበት አየር ማረፊያ አውሮፕላን ላይ ከተጫነ በኋላ ተጓጉዞ መድረሻው ቦታ ያለው አየር ማረፊያ ላይ እስከሚደርስ ድረስ ወይንም ከተራገፈ በኋላ ያሉት 30 ቀናት ሲያልቁ ውሉ ይቋረጣል፡፡
 • ይህ ውል የፖስታ ቤት እሽግ መልዕክቶችን አይሸፍንም፡፡
 • ሌሎች ጉዳዮችና በአደጋ ጊዜ የሚያስፈልጉ መረጃዎች ከላይ በተራ ቁጥር 1 ከተጠቀሰው ጋር ተቀራራቢ ናቸው፡፡

3.  በየብስ ላይ ብቻ ለሚጓጓዝ ንብረት የሚሰጥ ሽፋን

ይህ ውል በራሱ በ2 መልኩ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እነዚህም ውስንና ሰፊ ተብለው በ2 ይከፈላሉ፡፡

3.1 ውስን ሽፋን

 ይህ የውል ዓይነት ዕቃ በመጓጓዣ ተሽከርካሪ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሚጓጓዝበት ጊዜ ተሽከርካሪው ላይ በሚደርስ ድንገተኛ የመጋጨት፣ የመገልበጥ እና መንገድ ስቶ መውጣት ምክንያት ዕቃው ላይ ለሚከሰት የመቃጠል፣ የዝርፊያ እና ሌሎች ውድመቶች ሽፋን ይሰጣል፡፡

3.2 ሰፊ ሽፋን

ይህ ውል የሚጓጓዘው ንብረት ከታች የማይሸፈኑ ተብለው ከተዘረዘሩት ክስተቶች ውጭ ባሉ ማንኛውም ዓይነት አደጋዎች ቁሳዊ ጉዳት ከደረሰበት ሽፋን ይሰጣል፡፡

በውሉ የማይሸፈኑ ክስተቶች

 • ውሉ ላይ በነቂስ/በግለፅ ላልተጠቀሱ ዕቃዎች
 • ደንበኛው እያወቀ ለሚያጠፋው ጥፋት
 • ከንብረቱ/ከጭነቱ የተለመደና የሚጠበቅ ፍሰት፣ የክብደት/የቅርፅ መቀነስ/መቀየር፣ እርጅና እና መሰል ነገሮች
 • ደንበኛው/በሰራተኞቹ በተደረገ በቂ፣ ተገቢና ተመጣጣኝ ያልሆነ አጫጫንን ተከትሎ ለሚመጣ ጉዳት
 • ከንብረቱ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ጋር በተገናኘ መልኩ ለሚመጣ ጉዳት
 • በጉዞ መዘግየት ምክንያት ለሚመጣ ጉዳት
 • ደንበኛው እያወቀ ዕቃው/ንብረቱ ለጭነቱ በማይመጥን መጫኛ/ማጓጓዣ እና ኮንቴነር ላይ በመጫኑ ምክንያት ለሚመጣ ጉዳት
 • በደንበኛው ሰራተኞች በሚፈፀም ዝርፊያ (ማጭበርበር) ድርጊት
 • በዕቃ ማንሻ ብረቶች/ጋንች፣ በፈንጅዎች፣ በአሲዶችና መሰል አደገኛ ነገሮች በሚከሰት ጉዳትና የጥቅም መቋረጥ
 • ዕቃዎቹ ተገቢው መሸፈኛ ወይንም በተዘጋ ተሽከርካሪ ውስጥ ባልተቀመጡበት ሁኔታ በአየር ፀባይ ለሚደርስ ጉዳት
 • ከእቃዎቹ/ንብረቶቹ መግነጢሳዊ ችግር የተነሳ ለሚመጣ ጉዳት
 • ከጦርነት፣ አመፅና መሰል ነገሮች ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ጉዳት
 • ከአሸባሪነትና ከፖለቲካ ጋር ከተያያዙ ሁነቶች ጋር በተገናኘ ለሚፈጠር ችግር

የውል ጊዜ

 • የውሉ ጊዜ ዕቃው ከተሽከርካሪው ላይ ከተጫነበት ጊዜ አንስቶ እስከሚራገፍበት ጊዜ ድረስ ይሆናል፡፡

በውሉ መፈፀም ያለባቸው ሁኔታዎች

 • ደንበኛው ለንብረቱ ተገቢውን ጥንቃቄና ክትትል ማድረግ ይኖርበታል
 • ደንበኛው ዕቃው ከመጓጓዙ በፊት የቅድመ ምርመራ ማስደረግና ሪፖርት ማድረግ ይኖርበታል፡፡
 • በተቻለ አቅም ዕቃጫኝ መኪናውን መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልተቻለ ግን ሁሌ በሚቆምበት ጊዜ አስተማማኝነቱ በተረጋገጠ የተዘጋ ቤት/ግቢ ውስጥ መሆን ይኖርበታል፡፡

በአደጋ ጊዜ መደረግ ስላለበቸው ሁኔታዎች

 • ድርጅቱ በውሉ መሰረት በሚሸፈን አደጋ ለሚመጣ ጉዳት ካሳ ይከፍላል
 • አደጋ በሚፈጠር ጊዜ ደንበኛው በሚቻለው አቅምና በተገቢው መንገድ የሚደርሰውን ውድመት ለመቀነስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
 • አደጋው/ጉዳቱ በሚፈጠርበት ጊዜ ደንበኛው ለድርጅቱ በአስቸኳይ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡
 • ለሚመለከተው አጓጓዥ ስለጉዳቱ ማሳወቅና በፅሁፍ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተጎዱ ዕቃዎች እያሉ ለአጓጓዡ መልቀቂያ መስጠት አይገባም፡፡
 • ደንበኛው አደጋው/ክስተቱ በመርማሪዎች እንዲመረመር ማድረግ አለበት፡፡

ማሳሰቢያ፡- ይህ ፅሑፍ ስለ ዋስትናው አይነት ማብራሪያ ለመስጠት የቀረበ እንጂ በሕግ ፊት የሚፀና ውል አይደለም፡፡