የሰራተኛ ጉዳት ካሳ ዋስትና (Workers Compensation Insurance)

ይህ ውል አንድ ሰራተኛ በስራ ቦታው ላይ እያለ በስራ ጊዜ እና በተመደበበት ስራ ላይ እያለ እንደ ኢትዮጵያ ህግ ከስራው ጋር በተያያዘ ለሚደርስ አደጋ፣ በስራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ፣ የአካል ጉዳት ወይም ሞት አሰሪው ተጠያቂ ለሚሆንበት ኃላፊነት ዋስትና ይሰጣል፡፡

 የዋስትና መጠን  

በውሉ መሰረት የሚሸፈነው ሁኔታ ወይም አደጋ ተከትሎ ከ12 ወር ባልበለጠ ጊዜ ለሚከሰት የአካል ጉዳት ወይም ሞት የካሳ ክፍያው እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

 • ለሞት፡- የ5 ዓመት ደመወዝ ሲሆን በእያንዳንዱ ሰው ዝቅተኛው 10 ሺህ ከፍተኛው ደግሞ 150 ሺህ ብር ይሆናል፡፡
 • ለቋሚ የአካል ጉዳት፡- ውሉ ላይ በተጠቀሰው የካሳ አፈፃፀም ዝርዝር መሰረት ይፈፀማል፡፡
 • ለጊዜያዊ ቋሚ የአካል ጉዳት፡- የደመወዙ የመጀመሪያው ብር 250 ሙሉውን ለ52 ሳምንታት የሚሰጥ ሲሆን ከብር 250 የሚበልጠው የደመወዙ ክፍል ግን 75 ከመቶ ይከፈላል፡፡ በአጠቃላይ በወር የሚከፈለው የካሳ መጠን ግን ከብር 1500 አይበልጥም፡፡ በዚህ መሰረት የሚፈፀመው እስከ 3 ወር ያለው ክፍያ ከቋሚ የአካል ጉዳት ክፍያ የማይቀነስ ሲሆን ከዚያ ያለፈው ግን ተቀናሽ ይሆናል፡፡
 • ለህክምና፣ ለመድኃኒትና መሰል ወጪዎች፡- ውሉ በሰው እስከ ብር 1200 ይከፍላል፡፡
 • ከላይ የተጠቀሱት ወሰኖች እንዳሉ ሆኖ የድርጅቱ አጠቃላይ ወጪ በአንድ ክስተት ከብር 2 ሚሊዮን አይበልጥም፡፡

ውል ለመግባት የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች

 • የሰራተኞች ዝርዝር፣ የሥራ ድርሻና ወርሃዊ ደመወዝ

በመሰረታዊ ውሉ የማይሸፈኑ ክስተቶች

 • በመሰረታዊ ውሉ ከማይሸፈኑ ክስተቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
 • ሆን ተብሎ የሚፈፀም የራስ ማጥፋትና ጉዳት፣ ድብድብ፣ ተላላፊ በሽታዎች፣ በመጠጥ እና በአደንዛዥ ዕፆች ምክንያት የሚመጣ ጉዳት፣ አደጋ ወይም ሞት
 • ሰራተኛው እንዲያውቅ በግልፅ የተደረገን የስራ ደንብ በመጣስ ለሚፈጠር ችግር
 • መድን ገቢው ሌላ ተጨማሪ ውል በመግባቱ ምክንያት ለሚፈጠር ተጠያቂነት
 • መድን ገቢው ለተዋዋለው ሌላ የስራ ተቋራጭ ያለበትን ኃላፊነት
 • ከጦርነትና መሰል ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ መልኩ ለሚመጣ ጉዳት፣ አደጋ ወይም ሞት

በውሉ መሰረት ተፈፃሚነት ስለሚኖራቸው ሁኔታዎች

በውሉ መሰረት ተፈፃሚነት ከሚኖራቸው ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

 • ደንበኛው አደጋና ከስራ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በሽታዎች እንዳይፈጠሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግና ተያያዥነት ያላቸውን አዋጅና ደንቦች መፈፀም ይኖርበታል
 • ማንኛውም የአረቦን ክፍያ የሰራተኛውን ደመወዝ ያማከለ ሲሆን በውሉ ዓመት መጨረሻ ላይ የተከፈለውን አረቦን መከፈል ከነበረበት አረቦን ጋር በማነፃፀር ልዩነቱ ለደንበኛው ወይም ለድርጅቱ የሚሰጥ ይሆናል
 • ደንበኛው ድርጅቱ ሳያውቀውና ሳይፈቅድ ማንኛውንም ዓይነት ካሳ በራሱ መክፈል አይችልም
 • ድርጅቱ ሳያውቅ መድን ገቢው የስራ ባህሪውን መጀመሪያ ከተጠቀሰው አንፃር የበለጠ ለአደጋ ተጋላጭ ወደሆነ ስራ መቀየር የውሉን ተፈጻሚነት ስለሚያስቀረው ከዚህ መቆጠብ ይኖርበታል፡፡
 • ውሉ በሚገባበት ጊዜ ለድርጅቱ የተሰጡት መረጃዎች የተሳሳቱ ወይንም በማንኛውም መልኩ ልክ ያልሆኑ ከሆነ ውሉን እንዳልተፈፀመ ያስቆጥሩታል፡፡ በመሆኑም በዚሁ ረገድ ጥንቃቄ ማደረግ ተገቢ ነው፡፡

የካሳ አፈፃፀምና በአደጋ ጊዜ መደረግ ስለሚገባቸው ነገሮች

 • መድን ገቢው አደጋ ወይም በውሉ መሰረት የካሳ ጥያቄ የሚያስነሱ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በተቻለ ፍጥነት ለድርጅቱ በፅሑፍ ማሳወቅ ይኖርበታል
 • ሞትና መሰል ከባድ ጉዳቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ለሚመለከተው የፖሊስ/ የፀጥታ አካል ማመልከት ያስፈልጋል
 • ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ የሚጠይቃቸውን እንደ ህጋዊ የህክምና ማስረጃ፣ ደረሰኞች፣ የደመወዝ መክፈያ ሰነድ እና የመሳሰሉትን ደንበኛው ማቅረብ ይኖርበታል
 • ድርጅቱ በውሉ መሰረት የሚገባውን የካሳ ክፍያ ደንበኛው ከፈቀደ ቀጥታ ለተጎጅው ሰራተኛ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ይህም ድርጅቱን ከኃላፊነት ነፃ ያደርገዋል፡፡
 • ደንበኛው አደጋውን ሊሸፍን የሚችል ሌላ የመድን ውል ካለው የድርጅቱ የኃላፊነት መጠን ከሌላው ውል ጋር በንፅፅር ይሆናል፡፡

ውል ስለመሰረዝ

 • ደንበኛው በማንኛውም ጊዜ ውሉን ማቋረጥ ሲችል ድርጅቱ ደግሞ የ30 ቀናት የቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ውሉን ማቋረጥ ይችላል፡፡

ማሳሰቢያ፡- ይህ ፅሑፍ ስለ ዋስትናው አይነት ማብራሪያ ለመስጠት የቀረበ እንጂ በሕግ ፊት የሚፀና ውል አይደለም፡፡