ሌሎች የዋስትና ዓይነቶች (Other Miscellaneous Insurances)

1. የህጋዊ ኃላፊነት ዋስትና

 ይህ ዋስትና ለመድን ገቢውን ህጋዊ ኃላፊነት ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን የሚከተሉትን ኃላፊነቶች ያጠቃልላል፡፡ የዋስትና መጠኑ እንደ ደንበኛው ፍላጎት የሚወሰን ይሆናል፡፡

  • የምርት ተጠያቂነት ዋስትና፡- መድን ገቢው ባመረተው ምርት ምክንያት ለሚመጣ ጉዳት ዋስትና ይሰጣል፡፡
  • የማህበረሰብ ኃላፊነት ዋስትና፡- መድን ገቢው ደንበኛ በማህበረሰባዊ ጉዳዮች ለሚመጣበት ህጋዊ ተጠያቂነት ዋስትና ይጣል፡፡

2. የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ዋስትና

ይህ ዋስትና ደንበኛው አንድን ስራ ሙያው በሚጠይቀው ስነ-ምግባርና ክህሎት መሰረት ስለመፈፀሙ ለማረጋገጥ የሚሰጥ የዋስትና ዓይነት ነው፡፡ የዋስትና መጠኑ እንደ ደንበኛው ፍላጎት የሚወሰን ይሆናል፡፡

3. ቦንድ (Bond)

ይህ ዋስትና እንደአስፈላጊነቱ ብዙ ዓይነት ሲኖረው ከኮንስትራክሽን ስራዎች ጋር፣ ከጉምሩክ ግዴታ፣ ከዕቃ አቅርቦት ጋር ወ.ዘ.ተ በተያያዘ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ፡-

                3.1. የመልካም ስራ አፈፃፀም ዋስትና

 ይህ ዋስትና ስራ ተቋራጩ ያሸነፈውን ስራ   በተዋዋለበት መንገድና ጊዜ ስለማስረከቡ የሚሰጥ የዋስትና ሽፋን ነው፡፡ ይህን ውል ለማግኘት ደንበኛው ከዚህ በፊት ያጠናቀቃቸውን ስራዎች፣ የሒሳብ መዛግብቶች እና ሌሎች በድርጅቱ የሚጠየቁ መረጃዎችን ይዞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

3.2.  የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና

ይህ ዋስትና ተቋራጩ የስራ ማስኬጃ ቅድመ ክፍያ ለማግኘት እንደዋስትና የሚያገለግል የዋስትና ሽፋን ዓይነት ሲሆን በብዛት ከመልካም ስራ አፈፃፀም ዋሰትና ጋር አብሮ ይሰጣል፡፡ ይህን ውል ለማግኘት ደንበኛው ከዚህ በፊት ያጠናቀቃቸውን ስራዎች፣ የሒሳብ መዛግብቶች እና ሌሎች በድርጅቱ የሚጠየቁ መረጃዎችን ይዞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

3.3.  የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና

  ይህ የዋስና ዓይነት ደንበኛው በጨረታ ላይ ተሳትፎና አሸንፎ ስራውን ስለመስራቱ የሚሰጥ ማስተማመኛ ዋስትና ነው፡፡

3.4. የጉምሩክ ዋስትና

የዚህ የዋስና ዓይነቶች ብዙ ሲሆኑ ከተለመዱት ውስጥ ከቀረጥ ነፃ ለገቡ ዕቃዎች ተመልሰው ስለመውጣታቸው ማረጋገጫ ዋስትና እና ለአስመጪዎች በተለየ መልኩ የሚያገለግለው የቀረጥ የጊዜ ገደብ እፎይታ (ማለትም ተሽከርካሪዎቹ በሚሸጡበት ጊዜ የሚጠበቅባቸውን ቀረጥ ስለመክፈላቸው) የሚሰጥ ዋስትና ነው፡፡

3.5. የመያዣና የጥገና ዋስትናዎች

እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች ከግንባታ ስራዎች ጋር የተያያዙ ሲሆኑ ተቋራጩ ስራውን ካጠናቀቀ በኋላ የተሰራው ስራ እስከተወሰነ ጊዜ ገደብ ድረስ አፈፃፀሙን ጠብቆ ስለመቆየቱ የሚሰጡ ዋስትናዎች ናቸው፡፡

 

ማሳሰቢያ፡- ይህ ፅሑፍ ስለ ዋስትናው አይነት ማብራሪያ ለመስጠት የቀረበ እንጂ በሕግ ፊት የሚፀና ውል አይደለም፡፡