ከምህንድስና ጋር የተያያዙ የዋስትና ሽፋኖች (Engineering Insurance)

ይህ የዋስትና ሽፋን የተለያዩ የዋስትና ሽፋን ዓይነቶች ሲኖሩት ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

 • የስራ ተቋራጮች መገልገያ መሳሪያዎች ዋስትና
 • የኮንትራክሽን ስራ ተቋራጮች ዋስትና
 • የማሽነሪ/ፋብሪካ ተከላ ዋስትና
 • የቦይለር ዋስትና
 • የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ዋስትና

1. የስራ ተቋራጮች መገልገያ መሳሪያዎች ዋስትና (Machinery Breakdown)

የዚህ ውል መሰረታዊ ሐሳብ ለተለያዩ የኮንስትራክሽን ስራዎች ለሚውሉ ዕቃዎች በስራ ላይ ለሚደርስ ዉጫዊ ጉዳት በቂ እና ሙሉ ዋስትና መስጠት ነው፡፡ ይህ ዋስትና በውጫዊ ምክንያት በሚመጣ ድንገተኛና ባልተተነበየ አደጋ ምክንያት በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ዋስትና ይሰጣል፡፡ ውሉ የዋስትና ሽፋን የሚሰጠው መሳሪየዎቹ በስራ ቦታ ላይ እንዳሉና በተቀመጡበት ቦታ  ለሚደርስ ጉዳት ዋስትና ይሰጣል፡፡

በውሉ የማይሸፈኑ ክስተቶች/ሁኔታዎች

 • በየጊዜው ለስራው ሲባል የሚቀያየሩ መለዋወጫዎች ላይ ማለትም እንደመቁረጫ፣ ሰንሰለቶች፣ ባትሪ፣ ጎማና መሰል ነገሮች ላይ ለሚደርስ ጉዳት
 • በማንኛውም ማሞቂያ/ቦይለር፣ ወይም ባለ እምቅ ኃይል ምክንያት ለሚደርስ አደጋ
 • በግንባታ ቦታዎች ላይ ብቻ ጥቅም ላይ ካልዋሉ በቀር በተለመደ መንገድ ላይ እንዲንቀሳቀሱ ፈቃድ ለተሰጣቸው ተሽከርካሪዎች ሽፋን አይሰጥም፡፡
 • ማዕበል ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለሚደርስ የመስጠም አደጋ
 • መሳሪያው ከተሰራበት ዓላማ ውጭ ለየት ባሉ እንቅስቃሴዎች ላይ ሲሳተፍ ሽፋን አይሰጥም
 • በተጨማሪ ስምምነት ካልተሸፈነ በቀር መሳሪያው መሬት ውስጥ እየሰራ ለሚደርስበት አደጋ ሽፋን አይሰጥም
 • ከጦርነትና ተያያዥ ነገሮች፣ ከፖለቲካ፣ ከአመፅና መሰል ክስተቶች ጋር በተገናኘ ለሚደርስ አደጋ ሽፋን አይሰጥም
 • ከኒዩክሌርና መሰል ነገሮች ጋር በተያያዘ ለሚደርስ አደጋ ሽፋን አይሰጥም
 • ውሉ ከመፈፀሙ በፊት ማሽኑ ላይ ደንበኛው እያወቀው በነበረ ችግር ወይም ጉድለት ምክንያት ለሚመጣ ጉዳት
 • ደንበኛው ወይም ሰራተኞቹ ሆን ብለውና እያወቁ ለሚፈፅሙት ጉዳት ሽፋን አይሰጥም
 • የመሳሪያው አስመጭ ወይም አምራች በህግ ወይም በውል ተጠያቂ ለሚሆንበት አደጋ ሽፋን አይሰጥም
 • ማንኛውም ዓይነት የጥቅም መቋረጥን ሽፋን አይሰጥም
 • የኤሌክትሪክ፣ የመካኒካል፣ ዝገት፣ እርጅና እና የመሳሰሉትን አይሸፍንም፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን ተከትሎ ለሚመጣ ውጫዊ አደጋ ሽፋን ይሰጣል፡፡
 • ወቅታዊ ምርመራ ወይም ቆጠራ በሚካሄድበት ጊዜ ወይንም መሳሪያው የተለመደ ሰርቪስ በሚያደርግበት ጊዜ ለሚገኙ ጉዳቶች ሽፋን አይሰጥም፡፡

በውሉ መጠበቅ ስላለባቸው ሁኔታዎችና በአደጋ ጊዜ መደረግ ያለባቸው ሁኔታዎች

 • ደንበኛው ሁሌም ቢሆን አደጋ እንዳይከሰት መከላከልና የመሳሪያው አምራች የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል
 • ደንበኛው መሳሪያው ላይ መሰረታዊ እና ተፅዕኖ የሚያመጣ ለውጥ በሚያደርግበት ጊዜ ወዲያውኑ ለድርጅቱ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ በሚሆን ጊዜ ድርጅቱ ሽፋኑን ወይንም አረቦን ክፍያን በሚመለከት ለውጦችን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ ሲባል ግን ደንበኛው የአደጋ ተጋላጭነትን የሚጨምር ማስተካከያዎች ያደርጋል ማለት አይደለም፡፡
 • አደጋ በሚደርስበት ሰዓት ወዲያውኑ ለድርጅቱ ማሳወቅ ከደንበኛው ይጠበቅበታል፡፡ አደጋው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በ14 ቀናት ውስጥ ላልተላከ/ላልተገለፀ አደጋ ድርጅቱ ኃላፊነት አይወስድም
 • ከዚህ በተጨማሪም ለሚመለከተው የፖሊስ/የፀጥታ አካል ዳዩን ማስመርመርና ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅበታል
 • ደንበኛው በአደጋው የሚመጣውን ጉዳት ለመቆጣጠርና ለመቀነስ የሚቻለውን ተገቢ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡
 • ደንበኛው አደጋውን ለድርጅቱ ካሳወቀና የድርጅቱ ሰራተኞች አደጋውን ከመረመሩ በኋላ ጥቃቅንና ቀላል የሚባሉ ጥገናዎችንና የዕቃ ለውጦችን ሊያደርግ ይችላል፡፡

የዋስትና መጠንና የካሳ አከፋፈልን በተመለከተ

 • የማንኛውም መሳሪያ መድን ሊገባለት የሚገባው ዋጋ የግድ መሳሪያውን በአዲስ መሳሪያ ለመተካት በሚያስችል መጠን መሆን አለበት፡፡ ይህም የዕቃውን ሙሉ ዋጋ ከነቀረጡና መሰል ወጪዎችን ያካትታል፡፡
 • በማንኛም መልኩ መሳሪያው መድን የተገባለት ዋጋ ከላይ ከተጠቀሰው ያነሰ በሚሆንበት ጊዜ ድርጅቱ ካሳ የሚፈፅመው በንፅፅር ይሆናል፡፡ ይህም በእያንዳንዱ ዕቃ ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡
 • ደንበኛው በውሉ ላይ የተጠቀሰውን የአደጋ መነሻ በራሱ ይሸፍናል ወይንም ከአጠቃላይ ክፍያው ላይ ተቀናሽ ይደረጋል፡፡
 • ለሚጠገኑ ጉዳቶች ድርጅቱ የማስጠገኛ ወጪውን ከነዕቃ መቀየሪያው ይሸፍናል፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚቀየሩ ዕቃዎች ላይ የእርጅና ተቀናናሽ አይኖርም፡፡ ሆኖም ግን የቅሪት አካሎች ተቀናሽ እንዳግባቡ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
 • ማስጠገኛ ወጪው መሳሪያው ከአደጋው በፊት በሚገኝበት ሁኔታ ካለው ዋጋ ከበለጠ ድርጅቱ መሳሪያው ሙሉ ለሙሉ እንደወደመ ይቆጥረዋል፡፡ ለሙሉ ውድመት ድርጅቱ መሳሪያው ከአደጋው በፊት በሚገኝበት ሁኔታ ያለውን ዋጋ የእርጅና እና የቅሪት አካል ተቀናናሽ ካደረገ በኋላ ክፍያ ይፈፅማል፡፡

ውል ስለማቋረጥ

 • ደንበኛው በማንኛውም ጊዜ ውሉን ማቋረጥ ሲችል ድርጅቱ ደግሞ የ7 ቀናት የቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ውሉን ማቋረጥ ይችላል፡፡

2. የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ዋስትና (Contractors All Risks)

የዚህ ዋስትና መሰረታዊ ዓላማ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች የኮንትራት ስራውን በሚሰሩበት ጊዜ በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት/መጉደል፣ ከስራው ጋር በተያያዘ ለሚነሳ የሦስተኛ ወገን የንብረት መጥፋት ወይም የአካል ጉዳት ሙሉ እና በቂ ዋስትና መስጠት ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ዋስትና በውል ዘመኑ ውስጥ በድንገት እና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት በውሉ ላይ ከዋስትና ሽፋኑ ውጭ ከተደረጉት ምክንያቶች ውጭ ለሚደርስ ጉዳት ዋስትና ይሰጣል፡፡ ለዚህ ዋስትና ሽፋን ከሚሸፈኒ የጉዳት ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-

 • እሳት፣ መብረቅና ፍንዳታ
 • ጎርፍ፣ ዝናብ፣ በረዶ እና አውሎ ነፋስ፣
 • የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት መደርመስና   በደለል መሞላት
 • ስርቆትና ዘረፋ
 • በሰራተኞቹ አቅም ማነስ፣ ከጥንቃቄ ጉድለት፣ ወ፣ዘ፣ተ በሆነ ምክንያት ለሚደርስ ጉደት ዋስትና ይሰጣል፡፡

3.  የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች/ፋብሪካዎች ተከላ ዋስትና (Contractors Plant and Machinery)

ይህ ውል የተለያዩ ፋብሪካዎችና ማሽነሪዎች በተከላ ወቅት ለሚደርስባቸው ጉዳት ሙሉ እና በቂ ሽፋን በሁሉም የግንባታ ቦታዎች የሚሰጥ ሲሆን ለውሃ ማሞቂያዎች፣ ለኤሌክትሪክ አስተላላፊዎች፣ ለማምረቻ አገልግሎት ለሚውሉ ማሽሪዎች ተከላ፣ ለነዳጅ ማጣሪያ መሳሪያዎች፣ ወ.ዘ.ተ ዋስትና ይሰጣል፡፡ ሽፋኑ በተራ ቁጥር 2 እንደተገለፀው ይሆንና ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ በተሳሳተ ዲዛይን ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት ሽፋን ይሰጣል፡፡

4.  ማሞቂያ/የቦይለር ዋስትና (Boiler And Pressure Vessels)

ይህ ውል ፋብሪካዎችና የተለያዩ ተቋማት የሚጠቀሙባቸው ማሞቂያ/ቦይለር ላይ የእሳት አደጋን ሳይጨምር ለሚደርስ ያልተጠበቀና ድንገተኛ አደጋ ዋስትና ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 3ኛ ወገን ላይ ለሚደርስ አደጋ እንደአስፈላጊነቱ ሽፋን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህ የዋስትና ዓይነት የማይሸፈኑ ክስተቶች ሲኖሩት ውሉ ላይ በዝርዝር ይጠቀሳሉ፡፡

5. የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ዋስትና (Electronic Equipment)

ይህ የዋስና ዓይነት በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ማለትም እንደ ኮምፒዩተር፣ ቴሌቪዥን፣ ሰርቨር እና በመሳሰሉት ላይ ለሚደርስ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ጉዳት ዋስትና ይሰጣል፡፡ ይህን ዋስትና ለማግኘት የእያንዳንዱ ዕቃ ዝርዝር ከነዋጋው መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ይህ የዋስትና ዓይነት የማይሸፈኑ ክስተቶች ሲኖሩት ውሉ ላይ በዝርዝር ይጠቀሳሉ፡፡

 

ማሳሰቢያ፡- ይህ ፅሑፍ ስለ ዋስትናው አይነት ማብራሪያ ለመስጠት የቀረበ እንጂ በሕግ ፊት የሚፀና ውል አይደለም፡፡